ምዕራብ ኦሮሚያ፡ በደምቢ ዶሎ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደለው ወጣት ማን ነው?

ካርታ

ትናንት ማክሰኞ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ አማኑኤል ወንድሙ የተባለ ወጣት በአደባባይ በመንግሥት ኃይል መገደሉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የአካባቢ የመንግሥት ባለስልጣናትም የወጣቱን መገደል አረጋግጠው፤ ወጣቱ ለሕዝብ እንዲታይ ተደረገ እንጂ በአደባባይ አልተገደለም ሲሉ አስተባብለዋል።

የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ወጣት አማኑዔል 'የአባ ቶርቤ' ቡድን አባል በመሆኑ 'እርምጃ ተወስዶበታል' በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የደምቢ ዶሎ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት በበኩሉ ሰዎችን ሲገድል በነበረው እና 'የአባ ቶርቤ' ቡድን አባል በሆነው ግለሰብ ላይ እርምጃ ተወሰደ ሲል በፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፏል።

የከተማው ጽ/ቤት በፌስቡክ ገጹ ላይም ወጣቱ ከመገደሉ በፊት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አትሟል።

በአካባቢው በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የ"ሸኔ" ቡድን እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች ቡድኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ በተደጋጋሚ ይወነጀላል።

በዚህ ቪዲዮ ላይ ምን ይታያል?

በዚህ የፌስቡክ ገጽ ላይ ወጣቱ ከመገደሉ በፊት ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥ ይታያል። ቪዲዮን እየቀረጸ የሚገኘው ሰው የወጣቱን ስም እና የትውልድ ስፍራውን ይጠይቀዋል።

እጁ ወደ ኋላ የታሰረው ወጣት አንገቱ ላይ ሽጉጥ ተንጠልጥሎ ይታያል። በወጣቱ እግር ላይ እና በዙሪያው ደም የሚታይ ሲሆን ልብሱም በጭቃ ተለውሷል።

አደባባይ ፊትለፊት የቆመው ወጣት ስሙ አማኑኤል ወንድሙ ከበደ እንደሚባል እና ትውልዱ ደምቢ ዶሎ ከተማ 07 ተብሎ በሚጠራ ስፍራ እንደሆነ ይናገራል።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎ ተከቦ ይታያል።

አማኑኤል ወንድሙ ከመገደሉ በፊት ከተቀረፀው ተንቀሳቃስ ምስል የተወሰደ

የፎቶው ባለመብት, Dembi Dolo City Administration Communucation

ወጣቱ ለምን ተገደለ?

የከተማው ኮሚውኒኬሽን ጽ/ቤት እንደሚለው ከሆነ ይህ ወጣት የመንግሥት ባለስልጣናት በመግደል የሚታወቀው "አባ ቶርቤ' የተሰኘው ህቡዕ ቡድን አባል ነበር።

ወጣቱ ትናንት በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊትም ንጋት ላይ ገመቹ መንገሻ የተባለ ግለሰብ በጥይት መትቶ ለማምለጥ ሲሞክር "በጸጥታ ኃይሎች ጠንካራ ትስስር እግሩን ተመትቶ ተይዟል" ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ከቀናት በፊት በደምቢዶሎ ከተማ የኦሮሚያ ብሮድካስቲን ኔትዎርክ ጋዜጠኛ የነበረውን ሲሳይ ፊዳ የገደለው የአባ ቶርቤ ቡድን ነው ሲል አክሏል።

የዓይን እማኝ ምን ይላሉ?

የደምቢዶሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ ወጣቱ በአደባባይ ሲገደል ማየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አማኑኤል ሕዝብ የሚወደው ልጅ ነበር" ካሉ በኋላ፤ በጥይት ተመትቶ ከተያዘ በኋላ "ሲገደል በዓይናችን አይተናል" ብለዋል።

እኚህ ነዋሪ እንደሚሉት ከሆነ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ አካላት ወጣቱ ለመያዝ ሲንቀሳቀሱ ወጣቱ ከአንድ ሱቅ እቃ እየገዛ ነበር ይላሉ። ይህ ነዋሪ በአደባባይ ከተገደለው ወጣት በተጨማሪ በተመሳሳይ ቀን ሌሎች ሁለት ወጣቶች በጥይት ተመትተው ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሌላ ስፍራ ስለመወሰዳቸው አውቃለሁ ብለዋል።

የቄለም ወለጋ ዞን የደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተሰማ ዋሪዮ በበኩላቸው ወጣቱ ቆስሎ ከተያዘ በኋላ ለሕዝብ እንዲታይ ተደረገ እንጂ በአደባባይ አልተገደለም ይላሉ።

"ተጠርጣሪ አይደለም" የሚሉት አቶ ተሰማ፤ ይህ ወጣት ሁለት ሰዎች በጥይት መትቶ እያመለጠ ሳለ በፀጥታ ኃይሎች በጥይት ተመትቶ መያዙን ይናገራሉ።

ወጣቱ ለፍርድ ሳይቀርብ ለምን መሰል እርምጃ ተወሰደበት ለሚለው ጥያቄ ወጣቱ 'ተጠርጣሪ አይደለም' ከማለት ውጪ አቶ ተሰማ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጡም።

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት የሚመለከታቸውን የክልሉን ባለስልጣናት ለማናገር ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

አቶ ተሰማ በደምቢዶሎ አካባቢ ከሰሞኑ በኦነግ ሸኔ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደነበረ ተናግረው፤ ወጣቱ አንገት ላይ የተንጠለጠለው ሽጉጥ ንጹሃን ዜጎችን እና የመንግሥት ኃይሎችን ሲገድልበት የነበረ ነው ብለዋል።

ቢቢሲ የዞኑ ፖሊስ ባልደረቦችን አነጋግሮ ያገኘው ምላሽ አቶ ተሰማ ከሰጡት አስተያየት ጋር ተመሳሳይ ነው።

ማክሰኞ ዕለት 'አባ ቶርቤ' ተብሎ በሚጠራው ቡድን ተመቱ ከተባሉት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አንዱ አቶ ገመቹ መንገሻ በመባል የሚጠሩ ባለሃብት መሆናቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ በወንጀል የተጠረጠረውን አማኑኤል ወንድሙ ከፍርድ ውጭ የተፈፀመበት ግድያ እንዳሳሰበው ገለጿል።

line

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ያለው የእስረኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ያሳስበኛል ማለቱ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ በጎበኛቸው የፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው ነው።

ተጠርጣሪዎችን በሕግ ከመዳኘት ይልቅ የፖለቲካ (የአስተዳደራዊ) ውሳኔዎች ሰለባ እንዲሆኑ ተድርጓል ብሎ ነበር።

አባ ቶርቤ ማነው?

"አባ ቶርቤ" የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም "ባለ ሳምንት" ማለት ነው። ይህ ቡድን በኦሮሚያ የተለያዩ ስፍራዎች ታጥቆ ከሚንቀሳቀሰው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው አካል ጋር ግንኙነት እንዳለው የክልሉ ባለስልጣናት ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሐመድ "አባ ቶርቤ ማለት የአሸባሪው ሸኔ የከተማው ክንፍ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በከተማ ደግሞ 'አባ ቶርቤ' እና 'ሶንሳ' ተብሎ የሚጠራ ቡድን አለው። እነዚህ ቡድኖች በተቻላቸው መጠን ግድያ በመፈጸም ሽብር ለመፍጠር የሚሞክሩ ናቸው ሲሉ ተናግረው ነበር።

አቶ ጅብሪል መሐመድ እንደሚሉት የዚህ ቡድን አባላት ምንም አይነት የተለየ ስልጠናም ሆነ መሳሪያ የላቸውም። የሚጠቀሙት ስልት፤ ማህበረሰቡን በመምሰል፤ ለማምለጥ በሚያመቻቸው ቦታ በድንጋት አደጋ አድርሰው ይሰወራሉ" ብለው ነበር አቶ ጅብሪል።

የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አባ ቶርቤ የሚባለው ቡድን በክልሉ በተለያየ ጊዜ በመንግሥት ባለስልጣናት፣ የጸጥታ ኃይል አባላት እና ንሑሃን ዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርስ መቆየቱን ይገልጻሉ።